Romans 13

ባለ ሥልጣናትን መታዘዝ

1ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። 2ስለዚህ፣ በባለ ሥልጣን ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር ሥርዐት ላይ ማመፁ ነው፤ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ። 3ገዦች ክፉ ለሚሠሩ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለሥልጣንን እንዳትፈራ ትፈልጋለህን? እንግዲያስ መልካሙን አድርግ፤ እርሱም ያመሰግንሃል፤ 4እርሱ ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ነገር ግን ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ምክንያቱም ሰይፉን በከንቱ አልታጠቀም፤ ክፉ የሚያደርገውን ለመቅጣት የቍጣ መሣሪያ የሆነ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። 5ስለዚህም ቅጣትን በመፍራት ብቻ ሳይሆን፣ ለኅሊና ሲባል ለባለሥልጣናት መገዛት ተገቢ ነው።

6ግብር የምትከፍሉትም ደግሞ ለዚህ ነው፤ ባለሥልጣናቱ፣ በዚሁ ተግባር ላይ የተሰማሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና፤ 7ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ።

ጊዜው ተቃርቧልና ተዋደዱ

8እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ባልንጀራውን የሚወድድ እርሱ ሕግን ፈጽሟልና። 9“አታመንዝር”፣ “አትግደል”፣ “አትስረቅ”፣ “አትመኝ” የሚሉትና ሌሎችም ትእዛዞች ቢኖሩም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በዚህ በአንድ ሕግ ተጠቃልለዋል። 10ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ መፈጸሚያ ነው።

11ዘመኑን በማስተዋል ይህን አድርጉ፤ ከእንቅልፋችሁ የምትነቁበት ጊዜ አሁን ነው፤ መዳናችን መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ወደ እኛ ቀርቧልና። 12ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው። ስለዚህ የጨለማን ሥራ ጥለን፣ የብርሃንን ጦር ዕቃ እንልበስ። 13በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን። 14ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ
ወይም ለኀጢአተኛ ተፈጥሮ
በዐሳባችሁ አትመቻቹለት።

Copyright information for AmhNASV